Monday, December 2, 2013

የመጀመሪያ ደረጃ መደበኛ የፍትሐብሔር ክርክሮች አካሄድ (General outline for first instance ordinary civil proceedings)

የመጀመሪያ ደረጃ መደበኛ የፍትሐብሔር ክርክሮች አካሄድ (General outline for first instance ordinary civil proceedings)
  1.   የክስ አቤቱታ (ከሰነድና ከፅሁፍ ማስረጃ እንዲሁም ከማስረጃ ዝርዝር ጋር) ይቀርባል፡
  2. ተከሳሹ የመከላከያ መልሱን ይዞ እንዲቀርብ ይታዘዛል፡፡
  3. የመከላከያ መልስ (ከሰነድና ከጽሑፍ ማስረጃ እንዲሁም ከማስረጃ ዝርዝር ጋር) ይቀርባል፡፡ 
  4. የመከላከያ መልሱ ከቀረበ በኋላ የጽሑፍ ክርክሩ ያቆማል፡፡
  5. የጽሑፍ ክርክሩ ከቆመ በኋላ ክሱን ለመስማት ይቀጠራል፡፡
  6. በተቀጠረው ቀን ባለጉዳዮች ራሳቸው ወይም ወኪሎቻቸው ይቀርባሉ፡፡ 
  7. ባለጉዳች ከፅሑፍ አቤቱታቸው ጋር ያላቀረቡትን የፅሁፍ ማስረጃ ይዘው ይቀርባሉ፡፡  
  8. የጽሑፍ ማስረጃ ሁሉ በባለጉዳች ወይም በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ተጠቃሎ ይገባል፡፡ፍርድ ቤቱ ባለጉዳዮችን ወይም ወኪሎቻቸውን ይመረምራል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ከቀረበ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡
  9. በተደረገው ምርመራ ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ ካመነ ወዲያውኑ ውሳኔ ይሰጣል፡፡
  10.  ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ ካላመነ የክርክሩ ጭብጥ ይያዛል፡፡
  11.  ጭብጡ ከተመሠረተ በኋላ ክርክሩን መስማትና ማስረጃ መመርመር ይቀጥላል፡፡
  12. ለሁለቱም ወገን ምስክሮች መጥሪያ ይላካል፡፡
  13. የሁለቱም ወገን ምስክሮች ተሟልተው ይቀርባሉ፡፡
  14. ከሳሹ (በተወሰኑ ሁኔታዎች ተከሳሹ) ሙግቱን ይከፍታል፡፡
  15. ሙግቱን የጀመረው ወገን ምስክሮቹ የሚመሰክሩለትን ነጥብ በአጭሩ ያስረዳል፡፡
  16. ምስክሮች እውነት ለመናገር ይምላሉ ወይም እውነት እንደሚናገሩ ያረጋግጣሉ፡፡
  17. ሙግቱን የጀመረው ሰው ምስክሮቹን አንድ በአንድ አቅርቦ ዋና ጥያቄ ይጠይቃል፡፡ ፍርድ ቤቱ በማንኛውም ሰዓት አስፈላጊ የሆነ ጥያቄ ይጠይቃል፡፡
  18.  ሙግቱን የከፈተው ወገን ምስክሮቹን አሰምቶ ከጨረሰ በኋላ ለሌላኛው ወገን ምስክሮቹን የሚያስረዱለትን የመከላከያ ነጥብ በአጭሩ አስረድቶ በተመሣሣይ ሁኔታ ምስክሮቹን ያሰማል፡፡
  19.  ማስረጃ የመስማቱ ሂደት ሲጠናቀቅ ግራ ቀኙ የመዝጊያ ቃላቸውን ይሰጣሉ
  20.  በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ የፍርድ ውሳኔውን ይሠጣል

 ፍርድ
  1. የማስረጃ መሰማት ሥርዓት ተጣርቶ ካለቀ በኋላ ተከራካሪ ወገኖች የመዝጊያ (የማጠቃለያ) ቃላቸውን ይሰጣሉ፡፡ ሙግቱን የጀመረው ወገን መጀመሪያ ስለ ክርክሩ አጠቃላይ የመዝጊያ ቃሉን ይሰጣል፡፡ ከዚያ ሌላኛው ወገን ስለ ክርክሩ ያለውን አስተያየት በመዝጊያ ቃል ያቀርባል፡፡ በመጨረሻም ክርክሩን የጀመረው ወገን ለክርክሩ ያለውን ጠቅላላ የመዝጊያ ሐሳብ ያቀርባል
  2. የማስረጃ መሰማት ሥርዓቱ ተጣርቶ ካለቀና ከላይ የተጠቀሰው የመዝጊያ ቃል ከተሰጠ በኋላ ፍ/ቤቱ የፍርድ ውሳኔ ይሰጣል (ቁ.273)፡፡
  3. ለፍርድ ውሳኔው መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ ማስረጃዎች፤

1. የምስክሮች ቃል (ባለጉዳዮቹ አቅራቢነት ወይም በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ቀርበው ቃላቸውን የሰጡ፣ በምትክ ዳኛ የተሰበሰቡ የምስክሮች ቃል ወይም ከፍ/ቤት ውጪ በመሃላ የተሰጡ የምስክሮች ቃል)፣

2. በኤክስፐርቶች የተሰጡ ማረጋገጫዎች፣

3. በባለጉዳዮቹ ወይም በፍ/ቤት ትዕዛዝ የቀረቡ የፅሑፍ ማስረጃዎችና ሰነዶች፣

4. በምትክ ዳኛ የተሰበሰቡ ሌሎች ማስረጃዎ፣

5. ባለጉዳዮች በፅሑፍ ወይም ፍርድ ቤቱ በሚመረምራቸው ጊዜ የሚሰጧቸው የእምነት ቃላት፣

6. ፍ/ቤቱ በቁ.272 መሠረት ባደረገው ምርመራ የተገኙ መረጃዎች፣

7.  የታወቁ ጉዳዮች (Judicial notice)፣

8.  በሕግ የተወሰደ የህሊና ግምት (Legal presumption)፣

9.  ያንድን ነገር አፈጣጠርና ሂደት ማሳያ (Demonstration)፣


10. ፍ/ቤቱ በዓይነት እንዲመለከታቸው የሚቀርቡለት ነገሮች (Exhibits) ሊያጠቃልል ይችላል፡፡

4. የእነዚህ ማስረጃዎች ተቀባይነት (Admissibility) እና እውነተኛነት (Credibility) ፍ/ቤቱ ይወስናል፡፡
5.  ባለጉዳዮቹ ወይም ወኪሎቻቸው የመክፈቻና የመዝጊያ ንግግር ሲያደርጉ ወይም ምስክሮችን በሚመረምሩበት ጊዜ የሚናገሯቸው ቃላት እንደማስረጃ መወሰድ የለባቸውም፡፡
6.  ከላይ በክፍል (ሠ) (3) ከተጠቀሰው ውጪ ዳው ከችሎት ውጭ ያያቸው ወይም የሰማቸው ነገሮች ወይም ያገኛቸው ማስረጃዎች ለውሳኔው መሠረት መሆን የለባቸውም፡፡
7. የቀረበው ክርክር ከተሰማ በኋላ ፍ/ቤቱ ነገሩ እንዳለቀ ወዲያውኑ ወይም በአጭር ቀነ ቀጠሮ በሚወስነው ጊዜ በግልጽ ችሎት ፍርድ መስጠት አለበት (ቁ.180)፡፡
8. የፍርድ አሰጣጥ፣ የውሳኔው አፃፃፍና ፎርም በቁ. 181 እና 183 በተደነገገው መሠረት መሆን አለበት፡፡
9.  በአንድ የፍርድ ሐተታ ላይ የተያዘው ጭብጥ፣ ጭብጡ እንዴት እንደተወሰነና የተወሰነበት ምክንያት መገለፅ አለበት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሚሰጥ ፍርድ ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ዋነኛ ጉዳይ ባጭሩ የሚገልጽ መሆን አለበት (ቁ.182(1))፡፡
10. የመጀመሪያው ደረጃ ፍ/ቤት ተከራካሪዎቹ ወገኖች በዝርዝር ባላቀረቡት ወይም በግልጽ ባላመለከቱት ጉዳይ ላይ ፍርድ ለመስጠጥ አይችልም (ቁ.182(2))፡፡
11. በክርክሩ ላይ ከቀረቡት ብዙ ጭብጦች አንዱ ጭብጥ ብቻ ቢወሰን ሌሎቹንም ጭብጦች የሚያጠቃልል ከሆነ ክርክሩ ባንዱ ጭብጥ ብቻ ሊወሰን ይችላል፡፡ ካልሆነ ግን እያንዳንዱ ጭብጥ ለየብቻው ውሳኔ ማግኘት አለበት(ቁ.182(4))፡፡


2 comments:

  1. This comment has been removed by the author.

    ReplyDelete
  2. It is a very good introduction of the steps to follow in civil litigation.Disappointingly,there is a lot of discrepancy between the law and the practice.I will be posting some of these discrepancies and the steps in criminal litigation process soon on my blog https://ethiolaw-info.blogspot.com/

    ReplyDelete